"ከግጥምና ዜማ ደራሲው ዓለማየሁ ደመቀ ጋር ለእፍታ ማውጋት ጨዋታ ብቻ አይደለም፤ ትልልቅ ሀሳቦችን የያዙ ትናንሽ መጻሕፍትን እንደማንበብም ጭምር እንጂ። ከመጻሕፍትም የፍልስፍና መጻሕፍት። ደራሲው ለዓመታት በዘፈን ግጥሞቹ ሠላምና ፍቅርን ሲሰብከን እንደኖረው ሁሉ አሁን ደግሞ "ዮቶር (ከብላይ ካህን)" የተባለውን ልቦለድ ለ7 ዓመት ገደማ ጽፎ ካስቀመጠበት አንስቶ "እንካችሁ" ብሎናል። ልቦለዱ እንደሚጠበቀው ታሪክ ነግሮን የሚያበቃ አይደለም። ውስጣችንን ንጦ አንቀላፍቶ ያለውን ማዕበል ያስነሳል። ጨርሰን የምናበቃው ታሪክ አይደለም ያለው ፤ ጨርሰን እንጀምራለን። በእያንዳንዱ ምዕራፍና ገጽ ታሪክን ፣ ሀሳብን ፣ ፍልስፍናን ፣ ሥነልቦናን ፣ እምነትን ፣ ድብቁንና የተጠላለፈውን የሕይወትን ምሥጢር እንፈትሽበታለን። ከካህኑ ጋር አብረን በፈቃዳችን እንጓዛለን። ካህኑ ወደ ነበሩበት ሲመለስ የእኛ ጉዞ ግን አያበቃም ፤ ይቀጥላል። ከአንድ ደራሲና ድርሰቱ የሚጠበቀውም ይኸው ነው።"
ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ደራሲ እና ጋዜጠኛ"መንፈሳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተው ፍቅር ላይ ነው። ፍቅር ደግሞ የሰብአዊነት ቁልፍ ነው። ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ራሱን ለፍቅር ያስገዛል። በዘመናዊው ወይም በቁሳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ያላችሁ ተቀማጮች ያላገኛችሁት እርካታ እና ሰላም በመንፈስ ብትሰለጥኑ ኖሮ ሁሌም ከደጃፋችሁ ይኖራል፡፡ ወደ ውስጣችሁ፣ ወደ መሰረታችሁ በመመለስ ላይ ትጉ። ትናንት በገነነው ላይ ዛሬ ሌላው ገነነ፤ የትናንቱን ገናና በሚያስረሳው ዓለም አትወናበዱ። ዛሬ ተጨብጭቦለት ነገ በሌላው ጭብጨባ በሚዋጠው ወረተኛ ዓለም አትታለሉ።"
"ዛሬ ምስኪንና ተመፅዋች የሆነችው ኢትዮጵያ ለዚህ ሁሉ ችግር መድኃኒትና የመፍትሔም ምሳሌ ትሆን ዘንድ ነበር ጥንት የተፈጠረችው። ለዚህ በቆዳ ቀለም፣ በዘርና በሃይማኖት ለምትጨረስ ዓለም አንድ የመሆን ምሣሌ