ይኽ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሓፍ፡ ጣልያናዊው የዶሚኒካን መነኩሴ ቶማሶ ካምፓኔላ፡ "City of the Sun" በሚል ርእስ፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር፡ በ1603 በጻፈው አንድ ዩቶፕያዊ ሥነ-ጽሑፍ (utopian literature) ላይ የተደረገ የታሪክ ምርምር ውጤት ነው። በሰባት ምዕራፎች በተዋቀረው በዚህ መጽሓፍ ውስጥ፡ ፀሓፊዋ፡ ዶ/ር መስከረም ለቺሣ፡ በካምፓኔላ "City of the Sun" እና፡ በኢትዮጵያው የአክሱም ሥልጣኔ መካከል ያለውን ያልተነገረ ግንኙነት ትዳስሳለች። ዶ/ር መስከረም፡ በጣልያን ኅዳሴ ጊዜ እጅግ ተነባቢ የነበረው የዚህ የካምፓኔላ መጽሓፍ፡ የጽንሰ ሃሳቡ መሠረት፡ አክሱማዊው ሥልጣኔ መኾኑንም፡ በመረጃ በተደገፈ ሁኔታ ትተነትናለች። በተጨማሪም፡ ደራሲዋ፡ በካምፓኔላ ጽሑፍ ውስጥ ተጽዕኖዋቸውን ያሳደሩ ሌሎች ሥልጣኔዎችንም ትዳስሳለች። እነዚህም፦ የግሪኮ-ሮማን፣ የግብጽ፣ የባቢሎን እና የኢንዶ-ኢራንያን ሥልጣኔዎች ሲኾኑ፡ በፀሓይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት አምልኮ ላይ በተመሠረቱት በነዚህ ጥንታዊ ሥልጣኔዎችና በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ላይ በተመሠረተው የኢትዮጵያው ሥልጣኔ መካከል የነበረውን የክፍለ-ዘመናት ፍትጊያ ትዳስሳለች። እነዚህ ፍትጊያዎች፡ ለወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሥነ-ብዕላዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ-እውቀታዊ ቀውስ ያላቸውን አንድምታ፡ ከመውጫ መንገዶቹ ጋር፡ በመጽሓፉ የመጨረሻው ምዕራፍ ውስጥ ትጠቁማለች። መጽሓፉ፡ በመጀመሪያዎቹ የአውሮፓ ዩቶፕያዊ ሥነ-ጽሑፎች (Utopian Literature) እና፡ "የቄሱ ዮሓንስ አገር" ("Prester John's Land") ብለው በሰየሟት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ክርስቲያናዊ ሥልጣኔ መሃል ያለውን ግንኙነት ማጥናት ለሚፈልግ ኹሉ፡ እጅግ የሚመስጥ መጽሓፍ ነው።